Getas International Building 7th Floor
+251-114-16-32-73
Getas International Building 7th Fl.

የማዕድ ን ሚኒስቴር በሲሚንቶ አቅርቦት ላይ ለሚፈጠረው ችግር የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ተጠያቂ አደረገ

የማዕድ ን ሚኒስቴር በሲሚንቶ አቅርቦት ላይ ለሚፈጠረው ችግር የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ተጠያቂ አደረገ
  • አምራቾች ግን የሲሚንቶ ጉዳይን ከፀጥታ ችግር ጋር አያይዘዋልአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ900 እስከ 1‚000 ብር እየተሸጠ ነውየማዕድን ሚኒስቴር ከሲሚንቶ ምርትና አቅርቦት ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ያለው ችግር ምክንያቱ፣ ፋብሪካዎችም ሆኑ አምራቾች ማኅበር ለሲሚንቶ ምርት ትኩረት ባለመስጠታቸው እንደሆነ አስታወቀ፡፡ሚኒስቴሩ ከሳምንት በፊት ለ14 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በላከው ደብዳቤ በዚህ ወቅት ከሲሚንቶ ምርት፣ ከፋብሪካዎች የአስተዳደር ኃላፊዎች የቅርብ ክትትል ማጣት፣ እንዲሁም ከአምራቶች ማኅበር ውስንነት ጋር ተዳምሮ የሲሚንቶ ምርትና አቅርቦት ላይ ሰው ሠራሽ ችግሮች በስፋት እየታዩ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

    ችግሮቹን መሠረት አድርጎ የማዕድን ሚኒስቴር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉ ለድርጅቶቹ በተላከው ደብዳቤ ላይ የተመላከተ ሲሆን፣ በጥናቱም ተገኝቷል ያላቸውን ዋና ዋና ችግሮች አስታውቋል፡፡

    የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማኔጅመንት አባላትና የዘርፍ አመራሮች ለሲሚንቶ መመረት አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸው አውራው ችግር እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ እነዚህ አካላት የሲሚንቶ ምርት እጥረት እንዲፈጠር ተንቀሳቅሰዋል ተብሏል፡፡

    የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያለ በቂ ምክንያት ከአቅማቸው በታች እንዲያመርቱ ተደርገዋል ያለው የዳሰሳ ጥናት ውጤት፣ በተጨማሪም እነዚህ ፋብሪካዎች ያለ በቂ ምክንያትና ከዕቅድ ውጪ ምርት እንዲያቆሙ ተደርገዋል ብሏል፡፡

    የሲሚንቶ አምራች ማኅበር ለሲሚንቶ ምርት ትኩረት በመስጠት እንዲመረት አለማድረጉ ሌላ የተገለጸ ምክንያት ሲሆን፣ ማኅበሩ በተጨማሪ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ ባለማድረጉ በሲሚንቶ እጥረት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ጫና መፍጠሩ  በጥናት መለየቱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

    ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች የሲሚንቶ ኢንዱስትሪው በተፈለገ ደረጃ ላለማደጉ፣ እንዲሁም ምርታማነትን በተመለከተ የተሻሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይታዩ ምክንያት እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

    ሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም የፋብሪካዎቹ ዋና ኃላፊዎች በዳሰሳ ጥናቱ የተለዩና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ፈተው በአቅማቸው ልክ እንዲያመርቱ ትዕዛዝ ያስተላለፉት የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ በፀጥታና በጥሬ ዕቃ ግብዓቶች የተመለከተውን ጉዳይ ደግሞ የማዕድን ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልሎች ተቋማት ጋር አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ እንደሚወስድ በደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡

    በሌላ በኩል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር አመራር ለሪፖርተር እንደነገሩት፣ የሲሚንቶ አምራች ዘርፉ ከታመመ ቆይቷል፡፡ ይህ ዘርፍ ከሕመሙ እንዲያገግም ከተፈለገ በዘርፉ ውስጥ ድርሻ ያላቸው አካላት የራሳቸውን ግምት መናገራቸው ጥቅም የለውም፡፡

    የሲሚንቶ አቅርቦትን በተመለከተ በተለያዩ አከላት የሚሰጠው አስተያየት ሰበብ እንደ ማላከክ ከሆነ ቆይቷል ያሉት ባለሙያው፣ ከሰሞኑም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል የቀረበው አስተያየት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

    በደብዳቤው ላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ትክክል መሆን አለመሆናቸው እርግጠኝነት የሚጠይቅ ስለሆነ እሱን በመተው፣ በዚህ ወቅት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እየተቸገሩ ያሉት በምን ምክንያት ነው ቢባል የሚገኘው መልስ ከፀጥታ ችግር ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡ በዚህ ወቅት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቁልፍ የፀጥታ ችግር እንደሆነ ግልጽና የሚታይ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

    አንዳንድ ፋብሪካዎች የሲሚንቶ ጥሬ ዕቃ የሚያወጡበት ሥፍራ (ኳሪ ሳይት) ላይ 16 ሰዓት መሥራት ሲገባቸው በዚህ ወቅት እየሠሩ የሚገኙት ከአሥር ሰዓታት በታች እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ 25 ሠራተኞቹ የታፈኑበት ፋብሪካም ሙሉ በሙሉ እንደተዘጋና ሌሎች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች አሉ ተብሏል፡፡

    በግብዓት እጥረት ምክንያት የተዘጉ ፋብሪካዎች ከአንድ ወይም ከሁለት እንደማይበልጡ የተናገሩት የሪፖርተር ምንጭ፣ በዚህ ወቅት በሲሚንቶ ግብይት ላይ የተፈጠረው ዋናው የፀጥታ ችግር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

    ከፀጥታ ጋር በተገናኘ ያለው ችግር እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሚለውን በፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት ሊናገሩት የሚገባ እንደሆነ ያስረዱት ኃላፊው፣ ሆኖም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የችግሩ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

    ታጣቂ ኃይሎቹ ከፋብሪካዎቹ የአስተዳደር አካላት ጋር ይመሳጠራሉ ወይ የሚለውን እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ነገር ግን የመንግሥት ፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ግን ይህንን ተከታትሎና ለይቶ ተገቢውን ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡

    በአጠቃላይ በዚህ ወቅት ለሚስተዋለው የሲሚንቶ ዋጋ ማሻቀብ ምንጩ የምርትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ነው ያሉት ባለሙያው፣ አቅርቦቱን ያስተጓጎለው የፀጥታ ችግር እንዴት ሊፈጠር ቻለ የሚለውን የሚመለከተው አካል ማጣራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

    በሌላ በኩል የድንጋይ ከሰል የሚባለውን ግብዓት በአገር ውስጥ ለመተካት የተጀመረው ሥራ ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ያስታወቁት የሪፖርተር ምንጭ፣ ሆኖም በዚህ ወቅት የድንጋይ ከሰል የሚመጣባቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች  የፀጥታ ችግር ያለባቸው ስለሆኑ ምርቱ በበቂ ሁኔታ እንደማይመጣ፣ ከመጣም በብዙ ውጣ ውረድ የሚደርስ በመሆኑ ዋጋው ከፍ እንደሚል አስታውቀዋል፡፡

    በዚህ ወቅት ከሲሚንቶ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የደኅንነት ሥጋት በሆነው አካል ወይም ኃይል ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ኢንዱስትሪውንና ኢንቨስትመንቱን ማረጋጋት እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ በሲሚንቶ ምርት ላይ መንግሥት፣ ባለሀብት፣ የአስተዳደር አካላት፣ እንዲሁም የአምራቾች ማኅበራት ባለድርሻ አካላት እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡

    የሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር በፊናው መሥራት የሚገባውን ያህል አልሠራም ያሉት ኃላፊው፣ ብዙ ኢንቨስትመንቶችን ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ማኅበር ከዚህ የበለጠ የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ መትጋት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚህ ወቅት ላለው ችግር ዋነኛው ምክንያት ከማኅበሩ ጋር የሚያያዝ ነው ተብሎ እንደማይወሰድ አስታውቀዋል፡፡

    የማዕድን ሚኒስቴር በተሰጠው ተልዕኮ ላይ እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶች የማይካዱ ናቸው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ዘርፉን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት ዕውቅና እንደሚሰጡት ገልጸዋል፡፡ ከሲሚንቶ ጋር ተያይዞ በተላከው ደብዳቤ ላይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አመራር ጋር ውይይት ለማድረግ ማኅበሩ ቀጠሮ እንደያዘ ተገልጿል፡፡

    በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚገኙበት ወቅታዊ ሁኔታ ከላይ እንደተጠቀሰው ሆኖ ምርቱ በገበያ ውስጥ ያለው ወቅታዊ ዋጋ ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ እንደመጣ፣ ሪፖርተር ከሲሚንቶ ቸርቻሪዎችና ከግንባታ ባለሙያዎች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

    በጥር ወር የማዕድን ሚኒስቴር በቆላማው የአገሪቱ ክፍሎች የሚደረጉ የመስኖ ግድብ ግንባታዎች የገጠማቸውን የሲሚንቶ እጥረት ለመፍታትና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ፣ ለፕሮጀክቶቹ የሦስት ወራት የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት 802,972 ኩንታል ሲሚንቶ በአስቸኳይ እንዲቀርብ ለሲሚንቶ አምራቾች ዘርፍ ማኅበር ከማዕድን ሚኒስቴር የማሳሰቢያ ደብዳቤ መጻፉ ይታወሳል፡፡

    ከዚህ በተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቀድመው ገንዘብ የተቀበሉበት ከ2.6 ሚሊዮን ቶን በላይ ውዝፍ የሲሚንቶ ዕዳ ያለባቸው በመሆኑ ሌሎች ተጠቃሚዎች የሲሚንቶ ምርት ለማግኘት ረዥም ጊዜ እንደሚወስድባቸው፣ ጤናማ ያልሆነው የንግድ ግንኙነትም ለሲሚንቶ ምርት ዋጋ መናር ቀጥተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ከዚህ በፊት መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

    ከሰሞኑም ሪፖርተር በአዲስ አበባ በሚገኙ የሲሚንቶ ችርቻሮ መደብሮች ባደረገው ቅኝት የሲሚንቶ ምርት እጥረት እንደተከሰተ ያስተዋለ ሲሆን፣ ምርቱ በሚገኝባቸው የችርቻሮ መደብሮች የኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ከ900 እስከ 1,000 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

    በተለምዶ ዊንጌት በሚባለው አካባቢ ሲሚንቶ በመሸጥ የሚተዳደሩት አቶ እንድሪስ ከድር ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የሲሚንቶ እጥረት እንዳለ ሆኖ ገበያ ላይ የሚገኘው ምርት ዋጋ እጅግ በጣም የተጋነነ ስለሆነ በዚህ ወቅት መደበራቸውን ለመዝጋት ተገደዋል፡፡

    ምርቱ በተሻለ መጠን የሚገኘው አሸዋ ሜዳና ፉሪ በሚባለው አካባቢ እንደሆነ የተናገሩት አቶ እንድሪስ፣ ዋጋውም ከ900 እስከ 950 ብር እንደሚጠራ ገልጸዋል፡፡

    እጥረቱን በተመለከተ ምክንያቱን ለማወቅ ባደረጉት ጥረት ከሰሙት ውስጥ ፋብሪካዎች ምርት አቁመዋል የሚል እንደሚገኝበት፣ በማምረት ላይ የሚገኙ ጥቂት ፋብሪካዎችም ከአቅም በታች እያመረቱ ነው የሚል ምላሽ እንዳገኙ አቶ እንድሪስ አስረድተዋል፡፡

    የምርት አቅርቦት እጥረትና በዋጋ ማሻቀብ ሳቢያ የማያጓጓ ገበያ ባለበት ሁኔታ ውስጥ መሥራት የማይቻል ነው ያሉት አቶ እንድሪስ፣ ፋብሪካዎች በበቂ ሁኔታ ማምረት ጀምረው ዋጋው እስኪስተካከል ድረስ ቁጭ ብለው በተስፋ እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

Related Posts
Leave a Reply

Your email address will not be published.Required fields are marked *