Getas International Building 7th Floor
+251-114-16-32-73
Getas International Building 7th Fl.

የሲሚንቶ ዋጋ መናር

የሲሚንቶ ዋጋ መናር
  • ከ450 ብር በታች ከፋብሪካዎች እየወጣ ከአንድ ሺህ ብር በላይ ይሸጣል
  • ኮንትራክተሮችና ሸማቾች ዋጋው በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ300 ብር በላይ መጨመሩን
    ይናገራሉ

አዲስ አበባ፡- የሲሚንቶ ዋጋ በመወደዱ ለግንባታ መጓተትና ለአላስፈላጊ ወጪ ተዳርገናል ሲሉ ኮንትራክተሮችና ሸማቾች አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር በበኩሉ ሲሚንቶ በአማካይ ከ450 ብር በታች በሆነ ሽያጭ ከፋብሪካዎች ቢወጣም ገበያው ላይ አንድ ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቁሞ፤ ችግሩ በዋነኝነት በሕገወጥ ደላሎች የተከሰተ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው ኮንትራክተሮች እንዳረጋገጡት ቸርቻሪዎች ዘንድ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ950 ብር እስከ 1000 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል። የሲሚንቶ ዋጋ ንረቱ ገሃድ የወጣ ችግር መሆኑን ተዘዋውረን ተመልክተናል።

ኮንትራክተሩ አቶ በቀለ ኡርጋ እንደተናገሩት፤ የሲሚንቶ ዋጋ በመወደዱ ምክንያት መሸጫ ቦታዎች ላይ ስንጠይቅ አናገኝም። በጣም አስቸኳይ ግንባታ ቢኖር እንኳን ሲሚንቶ ብንፈልግ በተዘዋዋሪ ከደላሎች እንጂ ከሱቅ አናገኝም። ከደላሎች ሲገዛም ጠዋት የገዛንበት ከሰዓት ላይ ጨምሮ እናገኘዋለን ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።በአንድ ሳምንት ውስጥም እስከ 300 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

ይህም ለግንባታ መጓተትና ለአላስፈላጊ ወጪ ዳርጎናል። የሲሚንቶ ዋጋ መናርና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚታየው የሕገወጥ ደላሎች ገበያውን የመቆጣጠር አባዜ ካልተስተካከለ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ይበልጥ ከባድ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

ዋይቲኤስ በተሰኘው የኮንስትራክሽን ድርጅት የሚሰሩት ኢንጂነር በሱፍቃድ ሰለሞን በበኩላቸው ሲሚንቶ በመወደዱ የተነሳ ከቸርቻሪዎች ዘንድ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። ገንዘብ ይዘን እንኳን ለመግዛት የምንቸገርበት ወቅት አለ። የዋጋ መናሩ ሳያንስ በወቅት አለመገኘቱ ፈተና ሆኖብናል ሲሉ ተናግረዋል።

ኮንትራክተር አቶ ዐብይ አለሙ በበኩላቸው የሲሚንቶ ዋጋ በመናሩ የግንባታ ሥራዎች በወቅቱና በተያዘላቸው በጀት እንዳይጠናቀቁ እክል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። በየሰዓቱ የሚለዋወጠውን የሲሚንቶ ገበያ ማረጋጋት ካልተቻለ በኮሮና ዘመን የተጎዳው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ይበልጥ ይጎዳል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የደርባ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሲሚንቶ ከፋብሪካዎች ሲወጣ በአማካይ ከ450 ብር በታች ነው፤ ገበያው ላይ ግን ከእጥፍ በላይ እየተሸጠ ነው። ለዋጋ ንረቱንም ሕገወጥ ደላሎች የፈጠሩት ችግርና የምርትና አቅርቦት አለመጣጣም ዋነኛ ዋነኛ ምክንያቶች ሆነዋል።

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በግብዓት ዕጥረት ምክንያት ምርታቸውን በእጅጉ መቀነሳቸው በአቅርቦት ላይ የእራሱ የሆነ ጫና አሳድሯል የሚሉት አቶ ኃይሌ፤ በተለይ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከወለጋና ከቤኒሻንጉል እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የድንጋይ ከሰል ግብዓት ማጓጓዝ አስቸጋሪ በመሆኑ ፋብሪካዎች ውስን ምርት እንዲያቀርቡ አስገድዷል ብለዋል።

በዚህም በርካታ ፋብሪካዎች የምርት ሰዓታቸውን ቀንሰዋል። ለአብነት ደርባ ሲሚንቶን ብንወስድ አሁን ላይ የምሽት ፈረቃ ምርቱን አቁሞ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ብቻ እየሰራ ይገኛል። ሌሎቹ አምራቾች ላይም መጠኑ ይለያይ እንጂ ተመሳሳይ ችግር አለ። ይህም የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን በመፍጠሩ ገበያው ላይ ሲሚንቶ እንዲወደድ አንዱ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የአገር ውስጡ የድንጋይ ከሰል ለማግኘት ችግር በመፈጠሩ ከውጭ የሚመጣውን ለመጠቀም እየሞከርን ነው። ከውጭ የሚመጣው ደግሞ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ምክንያት የድንጋይ ከሰል ዋጋው በሶስት እጥፍ ጨምሯል። ከዚህ ባለፈ ግን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች አንዱ ግብአት የሆነው የከባድ ጥቁር ናፍጣ ዋጋ መጨመሩን አስታውሰዋል።

ይህ ሁሉ እያለ ግን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መሸጥ ካለባቸው ዋጋ ቀንሰው እያቀረቡ ይገኛል። ምክንያቱም ጦርነቱ ቀጣይነት አይኖረውም ከሚል እሳቤ የተነሳ በፍጥነት የተጋነነ ዋጋ ለመጨመር ፍላጎት የለንም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ፋብሪካዎች በአማካይ አንድ ኩንታሉን ሲሚንቶ በቅናሽ እያቀረቡ ቢሆንም ምርቱ ከፋብሪካ ከወጣ በኋላ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ ቢያንስ አምስት ሕገወጥ ደላሎች እጅ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ኃይሌ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሲሚንቶ ፍላጎት ከ11 ሚሊዮን ቶን በላይ ቢሆንም ፋብሪካዎች ግን ስምንት ሚሊዮን ቶን ነው እያመረቱ የሚገኙት። ደላሎቹ ይህንን የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ስለተረዱ የሲሚንቶውን ዋጋ የበለጠ እንዲንር በማድረግ ለግል ጥቅማቸው ያውሉታል።

በጉዳዩ ላይ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ውይይት መደረጉን ያነሱት አቶ ኃይሌ፤ ሚኒስቴሩ ሶስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። በዚህም የፋብሪካዎቹ ማኔጅመንት ማጠናከር፤ የሲሚንቶ አምራቾች ማኀበሩም ማጠናከር እና በሌላ በኩልም ከአቅም በታች የሚያመርቱትን አጠናክሮ በአቅማቸው እንዲያመርቱ ማድረግ ይገባል የሚል ሃሳብ ከሚኒስቴሩ መቅረቡን ተናግረዋል።

በአቅም ለማምረት ደግሞ የግብዓት እጥረቱን መፍታት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር አስፈላጊውን ማስተካከያ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። መከላከያ ሚኒስቴርም የተካተተበት ኮሚቴ ተዋቅሮ ግብአቶቹን ያለችግር ማቅረብ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የድንጋይ ከሰል ፍጆታ ለማቅረብ የሚረዳ ፋብሪካ ግንባታ ከሶስት ሳምንታት በፊት በዳውሮ ዞን መጀመሩ የሚታወስ ነው። የሲሚንቶ ዋጋ ንረቱን በተመለከተና በተለይም ደግሞ ህገወጥ ደላሎችን ለመቆጣጠር ያልተቻለበትን ምክንያት ለማወቅ ጉዳዩ ወደሚመለከተው ወደ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራዎችን ብናደርግም ጥረታችን አልተሳካም ።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም

Related Posts
Leave a Reply

Your email address will not be published.Required fields are marked *